በከተማው የሌማት ትሩፋት አምራቹ ለሸማቹ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረቡ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የሌማት ትሩፋት አምራቹ ለሸማቹ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረቡ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እያስቻለ ነው

ባሕር ዳር፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በባሕርዳር ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አምራቹ ለሸማቹ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ በማቅረቡ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ተጀምሮ በውጤታማነት የቀጠለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ የዜጎችን ህይወት በመለወጥ ተጨባጥ ለውጥ እያመጣ ነው።
መርሃ ግብሩ በውጤታማነት ከቀጠለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ አንዱ ሲሆን፤ ጥምር ግብርናን በማለማመድ ጭምር አዲስ የስራ ባህልን ፈጥሯል።
በባህርዳር ከተማ የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አይሸሽም ዓለሙ፤ ባላቸው 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሰው ሰራሽ የዓሳ ኩሬ በማዘጋጀት ዓሳ እያረቡ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማትና ዶሮ በማርባት ላይ እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልጸዋል።
አሁን ላይ 197 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችና በኩሬ ዓሳ ከማርባት ባሻገር ፓፓያ፣ ሰላጣና ቆስጣን ጨምሮ ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከዓሳ ኩሬው የሚወጣው ውሃ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ እንደ ማዳበሪያ ያገለግላል ያሉት አቶ አይሸሽም፤ የአትክልት ተረፈ ምርቱ ደግሞ ለዓሳ፣ ለዶሮና ለራሱ አትክልቱ ማዳበሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ለዘመናት በዘልማድ ያካሂዱት የነበረው የግብርና ስራ ውጤታማ እንዳላደረጋቸው አውስተው፤ በሌማት ትሩፋት መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ በዓመት ከፍጆታቸው አልፎ ምርቶቹን ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የገነት፣ ዮሴፍና ጓደኞቻቸው የዓሳ፣ ዶሮ ርባታና አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ገነት አባው በበኩላቸው፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አዲስና አዋጭ የስራ ዘርፍ ነው ብለዋል።
በየቀኑ 540 እንቁላል እያገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የዶሮዎችን ቁጥር አሁን ላይ ከአንድ ሽህ 200 በላይ ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዓሳ ኩሬ በማዘጋጀት ከሚያረቡት ዓሳ በግማሽ ዓመት ብቻ ከ600 ኪሎ ግራም ያላነሰ ዓሳ በማምረት አንዱን ኪሎ ግራም "ፊሊቶ" የወጣ ዓሳ በ500 ብር እየሸጡ መጠቀማቸውን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ከራሳቸው ቤተሰብ በተጨማሪ ለዘጠኝ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሃብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ውለታው አዳነ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ አዋጭ የስራ ዘርፍ ነው።
በዶሮ፣ በዓሳ፣ በወተት ልማት፣ በንብ እርባታና በእንስሳት ማድለብ ተግባር ለበርካታ ስራ አጥ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር በከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየተመራ ያለ መርሃ ግብር መሆኑን ተናግረዋል።
በዶሮ እርባታ ብቻ በ125 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 3ሺህ 780 ወገኖች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በቁጥር ከ62 ሚሊዮን በላይ እንቁላል በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በየቀኑ የሚመረተውን የላም ወተት ለሕብረተሰቡ ለማቅረብም የወተት ማህበራትን በማቋቋምና የመሸጫ ሱቆችን በመገንባት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
መርሃ ግብሩም አምራቹ ለሸማቹ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በውስን ቦታና በአነስተኛ ካፒታል በመነሳት ለትልቅ ደረጃ የሚያደርስ ዘርፍ ላይ በመሰማራት ራሱንና ቤተሰቡን ለመጥቀም በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ መስጀመራቸው ይታወሳል።