የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እና ከፍታ አንዱ ማሳያ ነው - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እና ከፍታ አንዱ ማሳያ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

የግብርና ሚኒስቴር አመራር እና ሰራተኞች "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።


 

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አውስተዋል።

በዚህም እስካሁን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ እድገት እያመጣ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት፣ ለአካባቢ ውበት፣ ለደንና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ እንዲካሄድ አቅጠጫ በማስቀመጥ እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ባለፉት ዓመታት ምርታማነት ማደጉን፣ የአፈር መሸርሸር መቀነሱን፣ የደን ሽፋን ማደጉን ጠቅሰው፥ መርሃ ግብሩ ትላልቅ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር መካሄድ ከጀመረ ወዲህ የተተከሉ ችግኞች ምርት መስጠት መጀመራቸውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሀብቷን ለልማት በማዋል የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠበቅ ላይ እንደምትገኝ አንስተው፥ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬትም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን እና የከፍታ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ግርማ ኃይሉ በበኩላቸው የአረንጓዴ ዐሻራ ስራ የሸገር ከተማን ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተሳተፉት በግብርና ሚኒስቴር የሚሰሩት አቶ እስራኤል ሎሃ፥ ዛሬ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ ብለዋል።


 

ወይዘሮ በላይነሽ ኩምሳ የተባሉት የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ በበኩላቸው ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ እንዲጸድቅ የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት።

የአረንጓዴ ዐሻራ አካባቢ እንዲጠበቅና የተራቆተ መሬት እንዲያገግም በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ተመስገን ደሳለኝ የተባሉ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም