ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው

ጉራፈርዳ፣ ሐምሌ 5/2017 (ኢዜአ)፡-ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆናቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተር ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በተጠሪ ተቋማት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ35 ሚሊዮን ብር ወጪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ለሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችና ሞዴል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
ለፕሮጀክቶቹ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተር ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው።
በእነዚህ ዓመታት በሕዝብና በመንግስት ትብብር በየዓመቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ገንብቶና አድሶ ለማስረከብ መቻሉን ተናግረዋል።
በእዚህም በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አክሊሉ፣ በልማት ተግባሩ ከፌዴራል እስከ ክልልና ቀበሌ ድረስ ያሉ ተቋማት ተሳትፎና እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም ልማቱን በማስቀጠል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በ33 ሚሊዮን ብር አምስት የገጠር ቤቶችና አንድ ሞዴል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በጉራፈርዳ ወረዳ እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
የሚገነቡት የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ የድርሻውን የሚወጣ ትውልድ ለመፍጠር ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር የእርስ በርስ መተጋገዝና መደጋገፍ ባህልን እያዳበረ መጥቷል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ ይህን የልማት ስራ ለማጠናከር በመምጣታቸው አመስግነዋል።
በክልሉ የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳድጉና የምግብ ዋስት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ገልጸዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በዘንድሮ የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ከ200 በላይ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች እድሳትና ግንባታ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የትውልድ ለትምህርት ንቅናቄን በስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ጠቁመው፣ ግንባታቸው እየተከናወኑ ያሉ ሰባት ሞዴል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በክረምቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት ተወካዮች በጉራፈርዳ ወረዳ በነበራቸው ቆይታ ችግኝ በመትከልም አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።