ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በፈጠረው ሀይቅ ዓሳን በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል - የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በፈጠረው ሀይቅ ዓሳን በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል - የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎች

አሶሳ፤ ሐምሌ 5/2017 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፈጠረው ሀይቅ ዓሳ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2018 ዓ.ም እንደሚመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።
ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ከግድቡ ሀይቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ዓሳ እያመረቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፈጠረው ሀይቅ ዓሳን ከሚያመርቱ የሸርቆሌ እና ሰዳል ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ኢዜአ ቆይታ ያደረገ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹም ግድቡ በፈጠረው ሀይቅ ዓሳ እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሳ ምርቱ ከተሰማሩ የሸርቆሌ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ አጅብ ሙሀመድ በህዳሴው ግድብ አማካኝነት ከተፈጠረው ሀይቅ ከሚያሰግሩት ዓሳ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
የዓሳ ምርቱን ለገበያ እያቀረቡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባለፈ ለምግብነት እየተጠቀሙ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዘካሪያ አጀሊ በበኩላቸው፤ በማህበር ተደራጅተው ዓሳን በማምረት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምርታቸውንም ለአሶሳና ለሌሎች አካባቢዎች በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ገልጸው በቀጣይ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሌላው ዓሳን አዘጋጅቶ ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው ኤሊያስ እና ጓደኞቹ ዓሳ አምራች ማህበር አባል ወጣት ደባሽ ትዜ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፈጠረው ሀይቅ ላይ የዓሳ ምርት በስፋት እያገኙ መሆኑን ተናግሯል።
በዓሳ ምርቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሞ ማህበሩ 40 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።
የሚያመርቱትን ዓሳ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በራሳቸው ተሽከርካሪ በማጓጓዝ እየሸጡ መሆኑንም ጠቅሷል።
በቀን እስከ 20ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውንና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በሰዳል ወረዳ በዓሳ ምርት ላይ የተሰማሩት አቶ ነጅብ መኪና ናቸው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት እና ዓሳ ግብዓት አቅርቦት ባለሙያ አቶ ገመቹ አየለ፣ በ2017 በጀት ዓመት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ 5ሺህ 895 ቶን የዓሳ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
በህዳሴ ግድብ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዓሳ ምርት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ጀልባ እና የዓሳ ማጥመጃ መረብ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
የሚመረተው ዓሳ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ትልልቅ ድርጅቶች ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውንም ባለሙያው አክለዋል።