የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢንሼቲቭ ሥራዎች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) ገለጹ።

የፌደራል እና የክልሎች የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ዛሬ በአርባ ምንጭ ጋንታ ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።


 

በዚሁ ጊዜ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እንደገለጹት በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢንሼቲቭ ሥራዎች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የአረንጓዴ ልማት ሥራው የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ፣ የከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።

በአርባ ምንጭ ጋንታ ተራራ ላይ ከአካባቢው አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር በመሆን አረንጓዴ ዐሻራ በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸው በዚህም ችግኝ ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነትን ትርክት ጭምር ተክለናል ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞች አርባ ምንጭ ከተማን ከጎርፍ ከመታደግ ባለፈ ዓባያና ጫሞ ሐይቆችን ከደለል በመከላከል ለሐይቆች ህልውና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ሳሙኤል ኡቦያ በበኩላቸው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በክልላቸው የአካባቢን ስነ-ምህዳርና ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ጉልህ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአርባ ምንጭ ጋንታ ተራራ ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋራ የአረንጓዴ ዐሻራ ማኖራቸው አብሮነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ አሚና ኢብራሂም፣ የአረንጓዴ ዐሻራ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ጋንታ ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን ማኖራቸው ይህንኑ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረ ወዲህ የዞኑ የደን ሽፋን እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ዛሬ የተተከሉ ችግኞች ለአርባ ምንጭ ከተማ ህልውና ትልቅ ጠቀሜታ የሚያስገኙ በመሆኑ በቀጣይ ህብረተሰቡን በማስተባበር እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ ዶይሳ ቀበሌ የአቅመ ደካማ እናት መኖሪያ ቤትን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ዛሬ በአዲስ መልክ ግንባታ አስጀምሯል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018  ዕቅድ ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም