የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ ሶስተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ከምሽቱ 4 ላይ አዘጋጇ ሞሮኮ ከሴኔጋል በፕሪስን ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ዛምቢያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኤል ባቺር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።  

ሞሮኮ አራት ነጥብ በመያዝ ምድቡን በአራት ነጥብ እየመራች ትገኛለች። ሴኔጋል በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛለች።


 

አዘጋጅ ሀገር ሞሮኮ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ሩብ ፍጻሜው ያሳልፋታል። ተሸንፋም ጥሩ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድል አላት።

ሴኔጋል ካሸነፈች በቀጥታ ሩብ ፍጻሜውን ትቀላቀላለች። አቻ መውጣት ወይም መሸነፍ ሁለተኛ አሊያም ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ እንድታልፍ ሊያደርጋት ይችላል።  

ዛምቢያ በምድቡ አራት ነጥብ በመሰብሰብ ተመሳሳይ ነጥብ ባላት አዘጋጇ ሞሮኮ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ማሸነፍ ዛምቢያ የማንንም ውጤት ሳትጠብቅ ወደ ሩብ ፍጻሜ እንድትገባ ያስችላታል።  ተሸንፋ ወይም አቻ ወጥታ በሂሳባዊ ስሌት ቀጣዩን ዙር የመቀላቀል እድል ልታገኝ ትችላለች። 

ሁለት ሽንፈት ያስተናገደችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

ማሸነፍ የኮንጎን ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድሏን ሊያለመልመው ይችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም