የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መደጋገፍንና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መደጋገፍንና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከናወናል

አበሽጌ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፡- የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መደጋገፍንና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከናወን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሀላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብርን ዛሬ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሀላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መደጋገፍንና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከናወናል ብለዋል።
በወረዳው ከ33 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል 15 የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም የችግረኛ ቤተሰብ አባላት ለሆኑ ለ2ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የኮሪደር መንደር እንደሚገነባ ያመለከቱት ሀላፊ ሚኒስትሯ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማትን ጨምሮ ሕብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን በማሳተፍ የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በተጀመረው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የጉራጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።