የመዲናዋ የ2018 በጀት 350 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋ የ2018 በጀት 350 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመዲናዋን የ2018 በጀት 350 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር አድርጎ አጸደቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አብዱልቃድር ሬድዋን፥ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት ዝርዝር ረቂቅ በጀት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ለ2018 በጀት ዓመት 350 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልጸው፥ በጀቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ108 ቢሊየን ብር ወይም የ45 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸዋል።
ከአጠቃላዩ በጀት ለመደበኛ ወጪ 91 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ሥራዎች 246 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ቀሪው 12 ቢሊዮን ብር ለመጠባበቂያ መሆኑን አብራርተዋል።
የካፒታል በጀት ከፍ እንዲል የተደረገው ለሰው ተኮር ሥራዎች፣ ለቤት ልማት፣ ለኮሪደር ልማት እና ለከተማ አስተዳደሩ ወሳኝ ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠት በማስፈለጉ መሆኑን አንስተዋል።
በጀቱ የከተማዋን ራዕይ፣ በሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችንና አዳዲስ የልማት ፍላጎቶችን፣ የታቀዱ አስተዳደራዊ ማሻሻያዎችን፣ አገልግሎት የማዘመን ስራን በፍጥነትና በውጤታማነት ለመተግበር ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
ከአጠቃላይ በጀቱ ከ238 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከታክስ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ከ56 ቢሊየን ብር በላይ፣ ታክስ ካልሆነ ገቢ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ፣ ከመንገድ ፈንድ 1.8 ቢሊየን፣ ከውጭ ብድርና እርዳታ 6 ነጥብ 98 ቢሊየን ብር እንደሚሰበሰብ ጠቅሰዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በረቂቅ በጀቱ ላይ በመወያየት በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል።