ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የሠራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ የሚያጠናክሩ ብቁ ሙያተኞች እያፈራ ነው - ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የሠራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ የሚያጠናክሩ ብቁ ሙያተኞች እያፈራ ነው - ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ የሚያጠናክሩ ብቃትና ሥነ-ምግባር ያላቸው ሙያተኞች እያፈራ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና፣ በጤና ሳይንስ፣ በቢዝነስ እና በኃብት አስተዳደር እንዲሁም በሌሎች የትምህርት መርኃ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዛሬው ተመራቂዎች ኢትዮጵያ በየዘመኑ ጀግኖችን የምታፈራ ሀገር ለመሆኗ ትልቅ ማሣያ ናችሁ ብለዋል።
የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሰለጠነ የሠራዊት አባላትንና ሲቪል አመራር በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በዚህም በእውቀት፣ በዓላማና በሙያዊ ልህቀት የታነጹ ሙያተኞችን እያፈራ ይገኛል ብለዋል።
የሠራዊቱን የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ብቃት ለማላቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሙያተኞች እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ መልኩም በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሀገርና ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ስራ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
ተመራቂዎች በታማኝነት፣ በቅንነትና በስነምግባር ሀገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።
በምርቃት መርኃ ግብሩ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በ2025 ከአፍሪካ አምስት ምርጥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቋል።