በክረምት ህክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የጤና አገልግሎት ይሰጣል - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በ2017ዓ.ም የክረምት ህክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ። 

እስካሁን በተከናወነው የክረምት ህክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት 10 ሚሊዮን ዜጎች የነፃ የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን አመልክተው፤ 12 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም ተናግረዋል። 

ሀገር አቀፍ ነፃ የክረምት የጤና ምርመራ፣ የምክርና የሕክምና አገልግሎት መርሃ ግብር በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ ተጀምሯል። 

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተጠሪ ተቋማትና የጤና ተቋማት አመራር አባላትን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የምርመራና ህክምና ነጻ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የደም ልገሳ፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የቤት እድሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የችግኝ ተከላ ይከናወናል። 

በክረምቱ ወቅት ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የታቀደ መሆኑን ጠቁመው፤ 250ሺህ ችግኞችን መትከል፣ 17 ጤና ተቋማት እድሳት፣ 40 የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ለስድስት ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ፅዱ የጤና ተቋማት መፍጠር የሚያስችል የፅዳት ዘመቻ፣ የወባ መከላከል ስራና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት።

ከ2011ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም በተከናወነው የክረምት የህክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ10 ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት መሰጠቱንና ከ400ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ተናግረዋል። 

አምና በተደረገው የክረምት ህክምና በጎ ፈቃድ ከ400 በላይ የተበላሹ የህክምና መሳሪያዎችን በመጠገን ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝ እንዳሉት፤ በ2016 በክረምት በጎ ፈቃድ ሆስፒታሉ ነፃ የጤና ምርመራ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት፣ ደም ልገሳና ሌሎች ተግባራትን አከናውኗል። 

በክረምት በጎ ፈቃድ የተጀመረው መርሃ-ግብር በበጋም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ ለ2016 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች የዕውቅና መርሀ ግብር ተካሂዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም