በከተማዋ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትልተደርጓል

አዳማ፤ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል መደረጉን የከተማዋ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ።

የከተማዋ ምክር ቤት 12ኛ ዓመት ሁለተኛ የስራ ዘመን 48ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እመቤት ጂባ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሲወጣ ቆይቷል።

በተለይም የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የልማት ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ፣ የስማርት አዳማ ፕሮጀክት ውጤታማነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል እንዲሆን በማስቻል ረገድ ምክር ቤቱ ሚናውን በአግባቡ ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህም በመሆኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የቻሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አውስተዋል።

በከተማዋ የተጀመሩ አገልግሎትን የማዘመንና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በቀጣይም የምክር ቤት አባላቱ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

ለምክር ቤቱ የበጀት ዓመቱን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፤ በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎት ያማከሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን  ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና አገልግሎትን በማዘመን ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው የጎጆ ኢንዱስትሪን ጨምሮ ከ51 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሲሆን በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ዝሪያ ማሻሻል፣ በዶሮ፣ በዓሣና በከብት ማድለብ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በከተማው ከ3 ሺህ 500 በላይ ሼዶች ተገንብተው ለወጣቶች፣ ማህበራትና አርሶ አደሮች መተላለፋቸውን ጠቅሰው ይህም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ለማሳካት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጽዳት፣ በውበትና አረንጓዴነት ላይ በተሰራው ስራ ከተማዋ የተሻለ ገጽታ እየተላበሰች መሆኗን ተናግረዋል።

የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ በተሰራው ስራ በበጀት ዓመቱ ከ12 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር  በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ድህነትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ያላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ በተሰራው ስራ 171 ፕሮጀክቶች ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።

የመሬት ሀብትን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል በተሰራው ስራ የካዳስተር ምዝገባን በማጠናቀቅ ዘመናዊ የመሬት አስተዳድር ስርዓት እውን ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም