የኢትዮጵያ ታዳጊዎችና ወጣቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታዳጊዎችና ወጣቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለፁ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች 4ኛውን የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና በሳይንስ ሙዚየም አስጀምሯል።


 

በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሰልጣኞችና የሰልጣኞች ወላጆች ተገኝተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ለማብቃት በክረምት ስልጠና እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር እውቀትና ችሎታ እንዲያዳብሩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሀገራት ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ቁልፍ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በሁሉም መስክ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለመጠቀም ሀገር ተረካቢ የሆኑ ታዳጊዎችና ወጣቶች በዘርፉ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

በዘርፉ መሰረታዊ እውቀት ኖሯቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

በ4ኛው ዙር የክረምት ስልጠና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 3ሺህ ታዳጊዎች መካከል 300ዎቹ መስፈርቱን አሟልተው ወደ ስልጠና መግባታቸው ተገልጿል።

ስልጠናው ለሁለት ወራት የሚሰጥ ሲሆን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረታውያን፣ ሮቦቲክስ፣ ፕሮግራሚንግና ሌሎች ትምህርቶችን ይወስዳሉ ተብሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም