በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ሃላፊ ማርቆስ ማቴዎስ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ነው።

በተያዘው የክረምት ወራት ከ4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ 12 ዞኖች እና ሦስት ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም በወጣቶች በሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ሊወጣ የሚችል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የህዝብና የመንግስት ሀብት ለማዳን ታቅዷል ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና ግንባታ እንዲሁም የጽዳትና ውበት ሥራዎችን ጨምሮ 14 የልማት ሥራዎች ተለይተው ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ክልል አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማካሄድ የህብረተሰቡን የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱንም  ጠቁመዋል።

በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር እያደገ መምጣቱን ጠቁመው ወጣቶች በልማት ሥራው በመሳተፍ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣት ሰላም ሐጎስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአዕምሮና የመንፈስ እርካታ ከመስጠት ባለፈ ለሀገርና ለወገን አስተዋጽኦ እንድናበረክት እያገዘን ነው ብላለች።

በበጋ ወቅትም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች መሳተፏን አስታውሳ በክረምቱም ይህን ተግባር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች በልማት ሥራ በመሳተፍ ለሌሎች ወጣቶች አርአያ ለመሆን እያስቻለን ነው ያለው ደግሞ የጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ነዋሪው ወጣት ስምኦን እንዳሻው ነው።


 

ዝናብና ጸሐይ ሲፈራርቅባቸው የነበሩ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ከችግራቸው መታደግ በገንዘብ የማይተመን ደስታ ይሰጣል ብሏል።

በተያዘው ክረምት በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የድርሻውን ለመወጣት ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግሯል።


 

በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ትዝታ ዘለቀ በበኩሏ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፈች መሆኑን ገልጻ፣ አገልግሎቱ በትውልድ መካከል ያለን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ስብዕናችንን በመልካም ለመገንባት እያስቻለን ነው ብላለች።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጋሞ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግበር ችግኝ በመትከል ባለፈው ረብዑ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም