ከጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 429 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ ከጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 429 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ ማዕድን ኃብት ልማት አስታወቀ።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ገቢ የተደረገው የወርቅ ምርት መጠን ከእቅዱ አንጻር የ2ሺህ 578 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለውም ተመልክቷል።

‎አንደ ሀገር የታለመውን የእድገትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ከተለዩት አምስት የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ የወርቅ ማዕድን ነው።

‎በዘርፉ የታለመውን ግብ ለማሳካት የተቀየሱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ መግለፃቸው ይታወሳል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳያነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጪ ገበያ የቀረበው ወርቅ ወደ 37 ቶን ከፍ ማለቱን ለምክር ቤቱ ማብራሪያ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

‎የጋምቤላ ክልል የማዕድን ኃብት ልማት ዋና ዳይሬክተር ኡጁሉ ጊሎ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በክልሉ የወርቅ ማዕድን ልማት ግብ ለማሳካት በተከናወኑት ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

‎በክልሉ በበጀት ዓመቱ 2ሺህ 850 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ከ5ሺህ 429 ኪሎ ግራም በላይ ገቢ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገው የወርቅ ማዕድን ከእቅዱ በ2 ሺህ 578 ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው መሆኑን ጠቁመው ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ5ሺህ 119 ኪሎ ግራም እንደሚበልጥ ገልጸዋል።

‎በክልሉ በበጀት ዓመቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት በዲማ፣ በጋምቤላ፣ በአቦቦና በመንጊሽ ወረዳዎች በባህላዊ፣ በልዩ አነስተኛና በትላልቅ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች የተመረተ ነው ብለዋል።

በዘርፉ የስራ እድልን ለመፍጠር በተደረገው ጥረትም ከ7ሺህ 680 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

‎በክልሉ በበጀት ዓመቱ የተሻለ የወርቅ ምርትና ግብይት ሊከናወን የቻለው ከክልል እስከ ወረዳ በተከናወነው የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም በክልሉ በተፈጠረው ሰላም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ በመግባታቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም