የበደሌ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ጽዱ ያደረጋት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የበደሌ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ጽዱ ያደረጋት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

በደሌ፣ሀምሌ 5/2017(ኢዜአ)፡- የበደሌ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ጽዱ ያደረጋት በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን የተሻለ ገጽታ እና ውበት ከማላበስ ባለፈ መንገድ በማስፋቱ ለእንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ጌታሁን ተፈሪ፤ የኮሪደር ልማት ከመገንባቱ በፊት መንገዶች ጠባብ እና የተጨናነቁ በመሆናቸው ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር ተናግሯል።
የኮሪደር ልማቱ ከተገነባ ወዲህ ሱቆችና ንግድ ቤቶች ጭምር ለስራ ምቹ ከመሆናቸው አልፎ ገጽታቸውም ተቀይሯል ብሏል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ኢሳያስ ጌታሁን በከተማዋ በመንገዶች ጥበት ምክኒያት ለትራፊክ አደጋ አጋላጭ ሁኔታዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
በተለይም የተሽከርካሪና የአግረኛ መንገድ መለየቱ አደጋን ከመቀነስ አልፎ መንገድ ላይ በእግር ለመራመድ የተመቸ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የከተማው የኮሪደር ልማት ስራ የበለጠ እንዲሰፋ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያመለከቱት ነዋሪው በስራው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የከተማው የኮሪደር ልማት ለእግረኛ ምቹ ሁነታ የፈጠረ፤ ከተማዋን ማራኪ ገጽታ ያላበሰ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዳንኤል ካሳሁን ናቸው።
''የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ የስራ እድል የፈጠረ እንዲሁም የከተማችንን ገጽታ የቀየረ ልማት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ብለዋል።
የበደሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ተሾመ፤ የኮሪደር ልማቱ በትኩረት ሲከናወን መቆየቱን እና በስራውም ትልቅ ለውጥ መታየቱን አስረድተዋል።
በከተማው በጅማ፣ በወለጋ እና በጎሬ መውጫ በሮች ተለይተው የኮሪደር ልማት ስራው ሲከናወን መቆየቱን ገልጸው የኮሪደር ልማት ስራውም የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ይገኛል ብለዋል።
እስካሁን ድረስ የተሰራው የኮሪደር ልማት ስምንት ኪሎሜትር የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንም አውስተዋል።