በሐረሪ ክልል ከ40ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይከናወናል - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ከ40ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይከናወናል - ቢሮው

ሐረር፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ከ40ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚከናወን የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
በክልሉ የገጠር እና ከተማ ወረዳዎች በአቅመ ደካማ ቤት እድሳትና ችግኝ ተከላ ሥራ በተጀመረው መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌቱ ወየሳን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ረምዝያ አብዱልዋህብ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ በየዓመቱ በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በተያዘው የክርምት ወራትም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ለማከናወን እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ነው የተናገሩት።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ከ40ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሳተፉ ጠቁመው በአገልግሎቱም 14 የትኩረት መስኮች ተለይተው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያድርጉ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት በበጎፈቃድ አገልግሎት ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም ወይዘሮ ረምዝያ አመልክተዋል።