በከተማዋ ተገንብተው የተመረቁ መሰረተ ልማቶች አገልግሎቶችን በቅርበት እንድናገኝ ያስችሉናል - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ ተገንብተው የተመረቁ መሰረተ ልማቶች አገልግሎቶችን በቅርበት እንድናገኝ ያስችሉናል - ነዋሪዎች

አዳማ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ ተገንብተው የተመረቁ መሰረተ ልማቶች አገልግሎቶችን በቅርበት ማግኘት እንደሚያስችላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግንባታቸው የተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶችን ለአገልግሎት ክፍት ሲያደርግ መቆይቱ ይታወቃል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደርም የከተማዋን ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሰረተ ልማቶችን ለአገልግሎት አብቅቷል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰሞኑን ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት መሰረተ ልማቶች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውን በማፋጠን ኑሯቸውን ለመለወጥ የሚያግዟቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከአዳማ ከተማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ጎሮ ወረዳ ነዋሪ ሸሪፍ ኢብራሂም እንደገለፁት ቀደም ባለው ጊዜ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው ባለመኖሩ እድሜያቸው ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የደረሱ ሕጻናት የትምህርት እድል በቅርበት አያገኙም ነበር።
ከአካባቢያቸው ራቅ ብሎ በሚገኝ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ወስዶ ለማስተማርም ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያለበት መንገድ ማቋረጥ ግድ ስለሆነ ለደህንነታቸው ስለምንሰጋ ቤት እናውላቸው ነበር ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኘ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው መገንባቱ ህጻናት ልጆች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተጠቃሚ መሆን እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱ መገንባት የትራንስፖርት ወጪና እንግልትን ያስቀረ ከመሆኑም ባለፈ በቅርበት ትምህርት ቤት በማግኘታቸው ለልጆቻቸው የወደ ፊት እጣ ፈንታም መልካም ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡ የመዝናኛ ማዕከላት በስራ የደከመ አዕምሯችንን ለማዝናናት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ያለው ደግሞ የደንበላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት እዮብ ክንዴ ነው።
የመዝናኛ ስፍራዎች በተለይ የከተማው ወጣቶች አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ ጊዜያቸውን በጥሩ እና ያማረ ስፍራ እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ለሚ ባለሚ በበኩላቸው አሁን በአካባቢያችን ያማረ መዝናኛ ስፍራ የተሰራበት ቦታ ቆሻሻ የሚጣልበትና ለእይታም የማይማርክ ነበር ይላሉ።
ስፍራው የከተማዋ ወጣቶችና አዛውንቶች ጭምር የሚዝናኑበት፣ እረፍት የሚያደረጉበትና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኙበት ሆኗል ብለዋል።
በደንበላ ክፍለ ከተማ የወንጂ የወተት ላሞችና የሥጋ ከብቶች ማድለቢያ ማዕከል ውስጥ የመስሪያ ቦታ ተጠቃሚ የሆኑት አርሶ አደር ተስፋዬ ካሳ፣ ከዚህ በፊት የእንስሳት ማድለብ ስራችንን የምናከናውነው በመኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ የወተት ላሞችና ለስጋ የሚሆኑ በሬዎች የሚያደልቡበት ዘመናዊ ማዕከል በማግኘታቸው መንግስትን አመስግነዋል።
የተሻለ የወተት ምርት የሚሰጡ ላሞችን ወደ ማዕከሉ በማስገባት በዘመናዊ መልኩ ለማርባት አቅደን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ መሰረተ ልማቶች መሰረታዊ አገልግሎት በቅርበት ማግኘት የሚያስችሏቸው ናቸው።