በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል - ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል - ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20/2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የግብርና ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞችም በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እና የከፍታ ጉዞዋ አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በዚህ ዓመት የመትከል ስራ በሁሉም አካባቢ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
እስካሁን በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ግርማ ኃይሉ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሸገር ከተማን ለማስዋብና በአካባቢ ጥበቃ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።