ኢጋድ የሴቶች የመሬት ባለቤትነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ የሴቶች የመሬት ባለቤትነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብታቸው እንዲከበር እና በአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ላይ የመሪነት ሚናቸው እንዲያድግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ።
ኢጋድ ከሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በኬንያ ናይሮቢ ስርዓተ ጾታ፣ መሬት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ግንባታ ላይ ሲያካሂድ የቆየው ቀጣናዊ ምክክር ዛሬ ተጠናቋል።
በምክክሩ ላይ ሴት የፓርላማ አባላት፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ተወካዮች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
ሁነቱ የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ የመሬት አስተዳደር እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ግንባታ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በአንድ መድረክ ያገናኘ ነው።
ውይይቱ የመሬት መብቶችን ማስጠበቅ እና ሴቶችን ያሳተፈ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ላይ ሁሉን አቀፍ የፖሊሲ ምክክር ማድረግ እና ቀጣናዊ ትብብርን የማጠናከር ውጥን ያነገበ ነው።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ምክትል ዋና ፀሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር ምክክሩ ሴቶች በመሬት ባለቤትነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ጠንካራ አቋም የተያዘበት መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣናው የሚገኙ ሴቶች ለመሬት ልማት፣ ግብርና እና ለዜጎች ደህነት መጠበቅ ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢገኝም በመሬት ባለቤትነት እና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው ነው ብለዋል።
ሴቶችን ማብቃት ለፍትህ፣ እኩልነት እና ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ቁልፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሴት ፓርላማ አባላት ቀጣናዊ ማዕቀፍ እና ቀጣናዊ የፖሊሲ ሰነድ ዝግጅት የውይይቱ ቁልፍ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
የአሰራር ማዕቀፎቹ በመሬት መብቶች እና በማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ላይ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታየባቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
ሀገራት ቀጣናዊ ማዕቀፎቹን የብሄራዊ እቅዶቻቸው ጋር አጣጥመው እንዲተገብሩና ከቀጣናዊ የአሰራር ስርዓቶች ጋር ስራቸውን እንዲያስተሳስሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የፓርላማ አባላቱ የለውጥ መሐንዲሶች ናቸው ያሉት ምክትል ዋና ፀሐፊው ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዲሆኑና በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ኢጋድ የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ እና በማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ቁርጠኛ እንደሆነ መግለጻቸውን ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ቀጣናዊ ምክክር ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ የተካሄዱ ምክክሮች ማጠቃለያ ነው።