በአርባምንጭ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬት ማሳያ ናቸው - ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)

አርባምንጭ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በአርባምንጭ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬት ማሳያ ናቸው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) ገለጹ።

የፌደራልና የክልሎች የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊዎች ማምሻውን የአርባምንጭ ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየምና የከተማዋን የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎች ጎብኝተዋል።

ከጉብኝት በኋላ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በአርባምንጭ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ማሳያ ናቸው።


 

በአምስት ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሀገር አልፎ በአህጉር ደረጃ ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ስታዲየሙ የአትሌቲክስ መሮጫና 25 ሺህ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን የተለያዩ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

አክለውም በህብረተሰብ ተሳትፎና በመንግስት ትብብር እየተገነባ ያለው ስታዲየም የሀገሪቱን የእግር ኳስ ዕድገት ከፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገለጸዋል።

በአርባምንጭ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማትም በፓርቲው እሳቤ መሠረት ከተሞችን ጽዱና ውብ እንዲሁም ለህዝብ ምቹ የማድረግ ትልም መገለጫ ሆኖ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማቱ ለአርባምንጭ ከተማ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ በመሆን ዘርፉን በማነቃቃት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።


 

ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም የልማት መስኮች የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአርባምንጭ ከተማ መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም