መጪው ምርጫ የትብብርና ፋክክር የዲሞክራሲ ባህል የሚገነባበት እንዲሆን በትኩረት ይሰራል - አቶ ፍቃዱ ተሰማ

ጎንደር፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ መጪው ምርጫ የትብብርና ፋክክር የዲሞክራሲ ባህል የሚገነባበት እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊዎች የተሳተፉበትና በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የግምገማ መድረክ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ማምሻውን ተጠናቋል።

አቶ ፍቃዱ ተሰማ የግምገማ መድረኩ ማጠቃለያን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ፓርቲው መጪው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን መላ አባላቱን የማዘጋጀት ስራዎቹን በትኩረት ያከናውናል ብለዋል።

ለዚህም የአባላት የስነ-ምግባር ደንቦችን በማዘጋጀት በምርጫው የትብብርና ፉክክር ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

አባላቱ በፓርቲው እሳቤዎች፣ መተዳደሪያ ደንብና አሰራሮች ዙሪያ ወጥና የተቀራረበ ግንዛቤ በመያዝ ተቋማዊ ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ አቅማቸውን የመገንባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የፓርቲው አደረጃጀቶች በልማት በሠላምና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደፓርቲና መንግስት ሰፋ ያሉ ውጤቶች የተመዘገቡበትና የማንሰራራት ዘመን በተጨባጭ የታየበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዓመቱ በፓርቲው ውስጥ የአመለካከት፣ የተግባር አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት የተጠናከረበት እንደነበርም ተናግረዋል።

ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት በጎ ጅምር የታየበት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የሀገሪቱን በጀት በትሪሊዮን እንዲጸድቅ ያስቻለና የእዳ ቅነሳ የተደረገበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራና የከተሞች ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

በሠላም ማስከበር ሂደቱ የታጠቁ ኃይሎች የመንግስትን የሠላም አማራጭ ተቀብለው ተሃድሶ በመውሰድ በስፋት ወደ ሠላማዊ ህይወት መመለሳቸውንም አስታውሰዋል።

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ፓርቲው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኃላፊው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም