ጠንካራ የሚዲያ ተቋም በመገንባት የልማት ስኬቶችን በቅንጅት ለህዝብ ማድረስ ይገባል

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 4/2017 (ኢዜአ)፡-ጠንካራ የሚዲያ ተቋም በመገንባት የልማት ስኬቶችን በቅንጅት ለህዝብ ማድረስ  እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018  ዕቅድ ግምገማ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ  ኃላፊው እንዳሉት፤ ጠንካራ የሚዲያ ተቋም በመገንባት በፓርቲው የተመዘገቡ የልማት ድሎችን ለህዝብ ለማድረስ በቅንጅት ይሰራል። 

ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሚዲያ በመፍጠር የተገኙ የልማት ድሎችን ለህዝብ ማድረስ ላይ  በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተዓማኒነት ባለው ተግባቦት የህዝቡን አንድነት ለማላላት የሚጥሩ ጽንፈኞች ሙከራን  እንዲከሽፉ መደረጉን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ  የተመዘገቡ አስደናቂ የልማት ውጤቶችን ለህዝብ ተደራሽ  በማድረግ በኩል ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ጽንፈኛ ኃይሎች የሚያካሄዱትን አሉታዊ እንቅስቃሴ አስቀድሞ ለመመከት ከመቼውም ግዜ በላይ መስራት ይገባል ብለዋል።

በፓርቲው የተመዘገቡ የልማት ድሎችን ከማሳወቅ አንፃር ማህበራዊ ሚዲያን በማጠናከር ተገቢውን ሽፋን እንዲያገኙ  እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ በሁሉም መመዘኛዎች የህዝብን አደራ ተቀብሎ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር) ፓርቲው ከጽንፈኝነት ይልቅ  ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን እንደሆነም አክለዋል።

''ጽንፈኞች የትርክትና የአጀንዳ የበላይነት የላቸውም'' ያሉት ኃላፊው ግልጽ ፕሮግራም፣ አስተሳሰብና እሳቤ ያለው ብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሁሉም ክልሎች የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በፓርቲው የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ወደ ህዝብ ይበልጥ ሊያደርሱ እንደሚገባም ኃላፊው አመልክተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018  ዕቅድ ግምገማ የተጠናቀቀ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎችም በነገው ዕለትም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ያከናውናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም