ማዕከሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የላቀ ችግኞችን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የላቀ ችግኞችን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ ነው

ቴፒ፣ ሐምሌ 4/2017 (ኢዜአ)፡- የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የላቀ የቅመማ ቅመምና ፍራፍሬ ችግኞችን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ።
ማዕከሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን በማዘጋጀት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲተከሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ (ዶ/ር) ማዕከሉ ዘንድሮ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በማዘጋጀት በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲተከሉ ለተለያዩ ክልሎች እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር እንዲተከሉ ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል ቡና፣ ካካዎ፣ አቮካዶ፣ ሻኔላና ሌሎችን ጨምሮ 8 ከደን ጋር በቀጥታ ተስማሚና ተያያዥነት ያላቸው እንደሚጠቀሱ ገልፀዋል።
ማዕከሉ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ባለው ጥረት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው የጎላ በምርምር የተደገፉ የሰብል አይነቶችን በማሰራጨት ረገድ ሚናውን እንዲሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።
በአካባቢው የሚመረቱ የቅመማ ቅመም ዓይነቶች ከዛፍ ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከቅመም ልማት ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ያነሱት ደግሞ የሸካ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዳምሰገድ ኃይለኢየሱስ ናቸው።
በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል በተሠራው ሥራ በዞኑ የደን ልማት ከምርታማነት ጋር አብሮ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም ቴክኖሎጂን በማስደገፍ የተገኙ ምርጥ የፍራፍሬ እና የቅመማ ቅመም ችግኞችን ከማዕከሉ በመውሰድ እየተከሉ መሆኑን ገልፀዋል።
ችግኞቹ በአርሶ አደሮች ጓሮ እየተተከሉ መሆኑን ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት በመስጠትም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ሥነ-ምህዳራዊ ጥበቃን እውን በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በወረዳው የፊዴ ቀበሌ አርሶ አደር ዓይናቸው ካሳሁን እንዳሉት፤ በየዓመቱ የግራቪላ ችግኞችን በመትከል ከሥሩ የቁንዶ በርበሬ ቅመም በመትከል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ2 ሄክታር በላይ የቁንዶ በርበሬ ቅመምን በግራቪላ ችግኞች ስር በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀው ዘንድሮም ግማሽ ሄክታር ያህል ችግኝ የሚተከልበት ቦታ ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡