የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እንዲገበያዩ መደረጉ የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ ያጠናክራል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እንዲገበያዩ መደረጉ የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ ያጠናክራል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እንዲመዘገቡና እንዲገበያዩ መደረጉ የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶችንና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የማገበያየት ሂደት በይፋ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ገበያው መጀመሩ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶችን በሰነደ መዋለ ነዋዮች አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ማቅረብ የሚያስችል ነው።
አጠቃላይ የመንግስትን ፋይናንስ አስተዳደር የማዘመን ሪፎርምን ለማሳካት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያዎች እንዲመዘገቡና እንዲገበያዩ መደረጉ የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።
የተጠናቀቀው በጀት አመት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያከናወነች ያለው የሪፎርም ስራ በስኬት የተጠናቀቀበት እንደሆነ በመግለጽ በቀጣይ በጀት አመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ጨረታዎች በገበያ መርሆች እንዲመሩ መደረጉን ተከትሎ የታዩት ለውጦች አበረታችና ውጤታማ ናቸው።
እነዚህ ማሻሻያዎች የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ከሚደረገው ጥረት በላይ ፋይዳ ያላቸው ሲሆኑ በኢኮኖሚው እንዲሁም በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ላይ ተአማኒነትና ተገማችነትን ለማስፋት የሚረዱ ናቸው።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው መንግስት ያጋጠሙ የምጣኔ ሃብት ችግሮችን በመፍታት የተረጋጋና ዘላቂ እድገት ማምጣት የሚያስችል ማሻሻያ ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
ከእነዚህ መካከል ግልጽና ተአማኒነት ያለው የካፒታል ገበያ መገንባት አንዱ ሲሆን የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣት፣ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች ውጤታማነትን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
በተመሳሳይ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ ከውጭ እዳ ጫና ጋር የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ገበያው ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልኩ የገበያው መጀመር ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ምጣኔ ሃብት ማሻሻያው እያከናወነች ባለው ሁሉን አቀፍ ጠንካራና ገበያ መር ምጣኔ ሃብት ግንባታ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢንቨስተሮች በገበያው ላይ በንቃት መሳተፍ የሚችሉበትን እድል የፈጠረና የመንግስት የእዳ አስተዳደር የማዘመን ሂደት ላይም ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች የገበያ መድረክ ሲሆን በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የተቋቋመ ነው።
የገበያው ዋና ዓላማ ውጤታማ የካፒታል ማሰባሰብ ስራዎችን በማጠናከር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት እድገት ግልጽና ደህንነቱ በተጠበቀ የካፒታል ገበያ ስራዎች መደገፍ ነው።