በመዲናዋ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን 219 በማድረስ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ተደርጓል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን 219 በማድረስ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች በቀጥታ እንዲደርስ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

3ኛዉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ተካሂዷል።

በስብሰባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።


 

በከተማዋ ሰላምና ጸጥታ፣ በተቋማት ሪፎርም፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማትና በማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች የተከናወኑ ተግባራትን ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት በበጀት ዓመቱ  ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም በተቋማት መፈጠሩን አንስተዋል።

347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በመከላከል በተቋማት ውስጥ ግልጽነት እንዲፈጠርና የተገልጋይ እንግልት እንዲቀንስ መደረጉን ገልጸዋል።

ይሁንና በአንዳንድ ተቋማት አሁንም ቢሆን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች በመኖራቸው  የማስተካከያ እርምጃ በመወሰድ ላይ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በሌብነትና ብልሹ አሰራር የተሳተፉ አመራርና ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና አዳዲስ በመገንባት እንዲሁም የምገባ ማዕከላትን በማስፋት ትውልድ ላይ ውጤታማ  ስራዎች መሰራቱንም ከንቲባዋ አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ በከተማ ግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ለ336 ሺህ የከተማዋ ሥራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከንቲባዋ አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተማዋን ከጎበኙ አንድ ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶች 143 ቢሊዮን ብር በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉን አመልክተዋል።

በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሀገር ወስጥ ጎብኚዎች ተዘዋውረው እንደጎበኟቸው እና በርካታ ገቢ እንዳስገኙም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋትና የኑሮ ወድነቱን ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ለተለያዩ ዘርፎች በመመደብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የገለጹት።

አዳዲስ የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት እና የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን 219 በማድረስ አምራቾች በቀጥታ ምርቶቻቸውን ለነዋሪዎች በተመጣጠኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር  አምራቹንም ሸማቹንም ተጠቃሚ አድርገናል ነው ያሉት።

በትራንስፖርት፣ በጤና መድህን፣ በዳቦ ምርትና በምገባ አቅርቦትን በመጨመር የኑሮ ጫናውን የሚያቃልሉ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

የገቢ አሰባሰብን በማሳደግ እና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድም በበጀት ዓመቱ ስኬት መመዝገቡን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ፣ በባለሃብቱ እና በህብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ የልማት ሥራዎችና የስፖርት ማዘወተሪያና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች መሰራታቸውን አስገንዝበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን በማስቀጠል በአዲሱ በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም