ፅዱ ኢትዮጵያን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ ነው-ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ - ኢዜአ አማርኛ
ፅዱ ኢትዮጵያን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ ነው-ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ፅዱ ኢትዮጵያን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ሁለተኛው ዙር “የጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ላይ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሚ፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ እንዳሉት፥ መንግስት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት፣ አረንጓዴ አሻራና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች በስፋት መሰራታቸውንም በማሳያነት አንስተዋል።
አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በብክለት ምክንያት በአካባቢና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ እና አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስስ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ላይ ክልክላ በማድረግ በሥርዓተ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሚያስችል አብራርተዋል።
አምራቾች ከማምረት ባሻገር ብክለትን በመከላከል ረገድ የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ በማድረግ በኩል እድል የሚሰጥ ሰለመሆኑ ገልጸዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፥ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የሚዲያ አካላት ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ አክለዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ ከምትሰራቸው የልማት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ፕላስቲክን በወረቀት ለመተካት የተጀመረው ስራም እንደ ሀገር አዲስ ልምድ እና የሚደነቅ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።
ለተግባራዊነቱና ለስኬቱም መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ግንዛቤ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
በብክለት ሳቢያ የሚደርሱ የጤና እክሎችን ቀድሞ በመከላከል የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በስልጠናው የተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ለህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት በኩል ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዜና ክፍል አርታኢ የሆነው ምንይችል አዘዘው፤ ጽዱ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተለያዩ ዘገባዎችን በመስራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አንስቷል፡፡
የዛሬው ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም በቀጣይ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለሚያከናውናቸው የዘገባ ስራዎች ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረለት ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ታምራት ተስፋዬ በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ የወጡ አዳዲስ ህጎችን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ የበኩላችንን መወጣት አለብን ብሏል።
ጽዱ ኢትዮጵያን ለማሳካት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ፣ የፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀም እና አወጋገድን በሚመለከት የተቀመጡ ድንጋጌዎች እና አተገባበሩ ላይ በትኩረት እንደሚዘግብም ጠቁሟል።