የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ወጣቶች ተሳትፏቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል

ወልዲያ ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፡- የወልዲያ ከተማን   ሰላም አፅንቶ  በዘላቂነት ለማስቀጠል ወጣቶች ተሳትፏቸውን ማጠናከር  እንደሚጠበቅባቸው  የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ  ገለጹ። 

የከተማ አስተዳደሩ ከከተማው ወጣቶች ጋር በሰላምና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ እንዳሉት፤ የአካባቢን ሠላም ለማፅናት ወጣቱ ከፀጥታ  አካላት ጋር በመተባበር የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።

በዚህም የህግ የበላይነትን በማስከበር ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸው፤ የተገኘውን ሰላም አስጠብቆ ዘላቂ ለማድረግ ወጣቶች ሲያበረክቱ  የቆዩትን  አስተዋጽኦ  ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በሰሜን ምስራቅ ዕዝ የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው፤ የመከላከያ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም ለማፅናት ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን  ገልጸዋል።

የወልዲያ ከተማ ወጣቶች ጽንፈኛውን አጥብቀው በመታገል ሲያበረክቱት የቆዩትን አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉም  መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በምክክር  መድረኩ  ላይ ከከተማዋ የተወጣጡ  ወጣቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም