በዞኑ የሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው - የደቡብ ኦሞ ዞን - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው - የደቡብ ኦሞ ዞን
ዲመካ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኦሞ ዞን የሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ለም መሬቶችና በቂ የሰው ኃይል እንዲሁም ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ እንደ ኦሞና ወይጦ ያሉ ወንዞች የሚገኝበት አካባቢ ነው።
የአካባቢውን ሀብቶች አቀናጅቶ በማልማት የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል።
በዞኑ ሳላማጎ ወረዳ በዲሜ ገሮ ቀበሌ በግብርና ልማት ከተሰማሩ የአካባቢው ወጣቶች መካከል ወጣት አለሙ ላስታ እንደገለፀው፥ ከዚህ ቀደም ኋላ ቀር በሆነ የእርሻ ዘዴ ሰብሎችን እና የቅባት እህሎችን ሲያለማ እንደነበረ ገልጿል።
አሁን ላይ በመንግሥት በተደረገላቸው የትራክተር ድጋፍ በሜካናይዜሽን እርሻ ሩዝ፣ ሰሊጥ፣ ማሾና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን በማልማት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግሯል።
የሳላማጎ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶማስ አስካም በበኩላቸው በአካባቢው እንደ ሰሊጥ፣ ሩዝ፣ ማሾ የመሳሰሉ የኤክስፖርት ምርቶች እና መደበኛ ሰብሎች በስፋት እየለሙ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በዞኑ የዳሰነች ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙዳ ቡራና የማሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርቆስ ተከስተበበኩላቸው በአካባቢያቸው በቂ የሰው ኃይል፣ ሊታረስ የሚችል ሰፊ ለም መሬት እንዲሁም ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞች መኖራቸውን አንስተዋል።
እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በተደረገው ጥረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን አንስተዋል።
በወረዳዎቹ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ገበያ ተኮር የአመራረት ዘዴን እንዲከተሉ በማድረግ የሙዝ፣ ጥጥ እና ማሾ ያሉ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን በስፋት በማልማት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ምንላርገው አዲሱ በበኩላቸው ዞኑ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ባደረገው ድጋፍ ወደ 10ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የአካባቢው አርብቶ አደሮች መሬት በሜካናይዜሽን እየለማ ይገኛል ብለዋል።
በሜካናይዜሽን እርሻውም የኤክስፖርት ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።