በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ርዕስ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ

ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 4/2017 (ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል በልማትና መልካም አስተዳደር ረገድ የተመዘገቡ  ውጤታማ ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ ገለጹ።

በጅግጅጋ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሂድ የቆየው የሶማሌ ክልል ሴክተር ቢሮዎችና የዞን አስተዳደሮች የ2017 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል። 


 

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤታማ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተከናውነዋል። 

ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት በግምገማው የተለዩ ጠንካራ አፈጻጸሞች ላይ በመመርኮዝ እና ደካማ ጎኖችን በማረም በክልሉ የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል። 

በቀጣይም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አመላክተዋል። 

መድረኩ ያስፈለገበትም የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ለመለየትና የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እቅድ አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ችግሮችን ለመፍታት ታልሞ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተጠያቂነትና ግልፅነትን ማጠናከር እንዲሁም አዲሱን በጀት ዓመት የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማጎልበት፣ የአስተዳደራዊ ቅልጥፍናን ለማሻሻልና በመንግስት ተቋማት ላይ የህዝብ አመኔታ ማጠናከር እንደሆነም አስረድተዋል ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም