የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ግብይት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ግብይት ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ግብይት ጀምሯል።
ይፋዊ የግብይት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንክ ፕሬዝዳንቶችና የልማት አጋሮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
የወጋገን እና የገዳ ባንኮች በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሰነዶቻቸውን በማስመዝገብና ሌሎች መስፈርቶችን በማሟላት ግብይታቸውን በይፋ አስጀምረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ግብይት መጀመሩ፥ የሪፎርም ስራዎችና የግሉ ዘርፍ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
ገበያው ኢኮኖሚውን የበለጠ በማነቃቃት፣ የበጀት ጉድለትን ለመሸፈንና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የገበያው መጀመር ኢንቨስተሮች ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁት የነበረ በመሆኑ አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን የሚከፍት ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፥ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ጠንካራ የካፒታል ገበያ መመስረት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
የገበያው መጀመር የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣትና ቁጠባን ለማበረታታት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው በቀጣይ ገበያውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ገበያው አስፈላጊ ዝግጅቶችና ሒደቶችን አልፎ በይፋ ግብይት መጀመሩን ገልጸዋል።
የግብይቱ መጀመር ለሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች የገበያ መድረክ ሲሆን በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የተቋቋመ ነው።
የገበያው ዋና ዓላማ ውጤታማ የካፒታል ማሰባሰብ ስራዎችን በማጠናከር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት እድገት ግልጽና ደህንነቱ በተጠበቀ የካፒታል ገበያ ስራዎች መደገፍ ነው።