አረንጓዴ አሻራ ግድቦች እና ሐይቆች በደለል እንዳይሞሉ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ግድቦች እና ሐይቆች በደለል እንዳይሞሉና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት"  በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ዛሬ ማለዳ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ምንጮችን በማጎልበት፣ የዝናብ ውሃን በማስረግ የከርሰ ምድር ውሃ ከፍ እንዲል በማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የገጸ ምድር የውሃ ሀብትን በመጠበቅም ግድቦች እና ሐይቆች በደለል እንዳይሞሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት  ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ችግኝ በመትከል ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታመነ ሃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው መርሃ ግብሩ የውሃ ሀብትን ለማጎልበት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ጎርፍ እንዳይከሰት እና አፈር እንዳይሸረሸር በማድረግ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ናቸው።


 

በ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል በማቀድ በመላ ሀገሪቱ የተጠናከረ የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም