የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ሀብት እንዲያንሰራራ እያደረገ ነው - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የስርዓተ ምህዳር ጥበቃን በማጠናከር የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ሀብት እንዲያንሰራራ እያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሠራተኞች በየካ ተራራ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘ እንደሚገኝ አንስተዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና እንድታገኝ ያስቻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ጠቀሜታዎችን በማስገኘት ላይ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የተራቆተ የአካባቢ ስርዓተ ምህዳር እንዲታደስ እና እንዲለመልም እያደረገ ነው ብለዋል።

የመሬት መንሸራተትን በመከላከልና የውሃ ሃብትን በመጠበቅ በኩልም ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን ጠቁመው በአፍሪካ በርሃማነትን ለመከላከል አርዓያነት ያለው ተነሳሽነት እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ ተመናምኖ የነበረው የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ሀብት እንዲያንሰራራ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር የተሳሰረ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መሳተፍ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር የማስረከብ ሀገራዊ አጀንዳ በመሆኑ፥ ሁሉም ህብረተሰብ ችግኝ በመትከል እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለመርሐ ግብሩ ስኬታማነት ከሐሳብ ማመንጨት እስከ ትግበራ እያደረጉ ላሉት የመሪነት ሚና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በዚህ በ7ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም