በመዲናዋ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እንተክላለን-ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እንተክላለን-ማህበራት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-በመዲናዋ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ወደ ተግባር መግባታቸውን የአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ማህበራት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በማቀድ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ማህበራትም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንደሚቀጥሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት እናትአለም እንዳለ ማህበሩ ከ500 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ጠቅሰው አባላቱ በአረንጓዴ አሻራ እና በበጎፍቃድ ስራዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበሩ አባል ሴቶች ባለፉት ስድስት ዙር መርሃ ግብር በርካታ ችግኞችን መትከላቸውንም አውስተዋል።
በዘንድሮው መርሃ ግብርም አባላቱን በማስተባበር 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሀፊ ኤርሚያስ ወንድሙ በበኩሉ ማህበሩ ከ280 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ጠቅሷል፡፡
አባለቱ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ በመትከል ከመሳተፋቸው ባለፈ ችግኝ በማፍላት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ2 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የሴቶችና የወጣት አመራሮቹ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ የእንክብካቤ ስራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።
በክረምቱ ወቅት የደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የቤት እድሳትና ሌሎች የበጎ ፍቃድ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።