የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው አለም ጋር በማገናኘት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው አለም ጋር በማገናኘት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሃኖይ ቪየትናም አዲስ በረራ በትላንትናው እለት ጀምሯል።

በበረራ ማስጀመሪያ መርሀግብሩ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የቪየትናም የንግድ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል።

አየር መንገዱ በሳምንት አራት ጊዜ ወደ ሃኖይ ቪየትናም የመንገደኞች በረራ ያደርጋል።


 

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ወደ ሃኖይ ቪየትናም የሚያደርገው የመንገደኞች በረራ የአገሮቹን ግንኙነት በጉልህ ያሳድገዋል።

አየር መንገዱ የስኬት ማሳያ ተቋም መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አየር መንገዱ እንደ ሀገር የተያዙ ኢኮኖሚያዊ እቅዶች እንዲሳኩ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አንስተዋል። 


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው አለም ጋር በማገናኘት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ የጀመረው በረራ በኢትዮጵያና በቬትናም መካከል ጠንካራ የትስስር እና ትብብር እድሎችን እንደሚፈጥር እና የንግድ፣ ቱሪዝም እና የባህል ልውውጥ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።


 

የበረራ መስመሩ በአፍሪካ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ መካከል ቀጥተኛ ትስስር እንዲኖር እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስትራቴጂካዊ መስፋፋትን በማጠናከር ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚያጎለብት መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

አየር መንገዱ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ እስያ እና ፓስፊክ አገሮች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ደዋኖ ከድር በበኩላቸው፤ አሁን የተጀመረው በረራ ለሁለቱ አገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም