በድሬዳዋ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አግዘዋል-ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አግዘዋል-ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ ፤ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡- በድሬዳዋ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ማገዛቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
በአስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ400 በላይ ቤተሰቦችን ከተረጂነት ማላቀቅ መቻሉም ተገልጿል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የማዘጋጃ ቤት እና የሴክተር ተቋማት የስራ አፈፃፀም እየተገመገመ ይገኛል።
ግምገማውን እየመሩ የሚገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ነባርና አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ መሰራቱን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም በገጠርና በከተማው የአስተዳደሩ ክላስተሮች የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች ከ400 በላይ ቤተሰቦች ከሴፍቲኔት ተረጂነት መላቀቃቸውን ገልጸዋል።
በገጠሩ የአስተዳደሩ ክላስተር ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ የተለያዩ ኢንሺየቲቮች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን በመግለፅ ።
እነዚህን ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ እህል ለማምረት 107 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በራስ አቅም ለአደጋ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረተሰቡ፣ ሠራተኛው እና አጋር አካላት በዓይነትና በገንዘብ በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።
በግምገማው መድረክ ላይ የተሳተፉት የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የሴክተር ኃላፊዎች፣ አማካሪዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች የቀረበውን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እየገመገሙ ናቸው።