ፅዱና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው-ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ) ፡-ፅዱና የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን በማድረግ ለትውልዱ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነትና የግንዛቤ ፈጠራ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ሁለተኛው ዙር “የጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ”  በሚል መሪ ሀሳብ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ላይ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

በመድረኩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታው ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።


 

ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ ከምትሰራቸው  የልማት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።

የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ፕላስቲክን በወረቀት ለመተካት የተጀመረው ስራም እንደ ሀገር አዲስ ልምድ እና የሚደነቅ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።

ለተግባራዊነቱና ለስኬቱም  መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ግንዛቤ የሚፈጥሩ መርጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

በብክለት ሳቢያ የሚደርሱ የጤና እክሎችን ቀድሞ በመከላከል የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ፥ መንግስት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት፣ አረንጓዴ አሻራና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች በስፋት መሰራታቸውንም በማሳያነት አንስተዋል።


 

አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በብክለት ምክንያት በአካባቢና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ እና አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስስ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ላይ ክልከላ በማድረግ በሥርዓተ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሚያስችል አብራርተዋል።   

አምራቾች ከማምረት ባሻገር ብክለትን በመከላከል ረገድ የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ በማድረግ በኩል እድል የሚሰጥ ስለመሆኑ ገልጸዋል።


 

የአካባቢ ጥበቃ ስራ የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፥ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የሚዲያ አካላት ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው  አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም