የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሰባተኛ ቀን ውሎ የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምዕራብ አፍሪካውያኑ ጋና እና ማሊ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በቤርካኔ ሙኒሲፓል ስታዲየም ይጫወታሉ።
ጋና በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በደቡብ አፍሪካ የ2 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዳለች። ማሊ በበኩሏ ታንዛንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ጋና በውድድሩ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርባታል። በአንጻሩ ማሊ ድል ከቀናት ሩብ ፍጻሜውን ትቀላቀላለች።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ እርስ በእርስ ተጫውተው ጋና ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ማሊ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል። በቀሪው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።
በጨዋታዎቹ ጋና 15 ግቦችን ከመረብ ጋር ስታገናኝ ማሊ 12 ግቦችን አስቆጥራለች።
ባላቸው የእርስ በእርስ ታሪክ ጋና የተሻለ የማሸነፍ ግምት ብታገኝም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የምትገኘው ማሊ ተጋጣሚዋን የመፈተን አቅም አላት።
በዚሁ ምድብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ታንዛንያ ከደቡብ አፍሪካ በሆነር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ደቡብ አፍሪካ በሶስት ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው። ታንዛንያ ያለ ምንም ነጥብ በአንድ የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ደቡብ አፍሪካ ካሸነፈች ሩብ ፍጻሜ ትገባለች። ታንዛንያ በውድድሩ የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ ጠንካራ ተጋጣሚዋን መርታት ይኖርባታል።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተው ደቡብ አፍሪካ ሶስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ደቡብ አፍሪካ በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ታንዛንያ ሶስት ግቦችን አስቆጥራለች።