ቀጥታ፡

የድሬዳዋ - መልካ ጀብዱ የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ድሬዳዋ ፣ ሐምሌ 04/2017(ኢዜአ) ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው የድሬዳዋ - መልካ ጀብዱ የአስፋልት መንገድ ግንባታ   እየተፋጠነ መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድሬዳዋ የመንገድ ጥገና ዲስትሪክት አስታወቀ።

መንገዱ በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት ሳይጠናቀቅ የተቋረጠ እና የመልካ ጀብዱ አካባቢ ነዋሪዎች የዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ እንደቆየም ተመላክቷል።


 

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፉአድ ንጉሱ ለኢዜአ  እንዳስታወቁት፤ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ  ወደ ግንባታ የተመለሰው የ2 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት በወሰን ማስከበር ምክንያት ሳይጠናቀቅ የተተወ ቀሪ ክፍል ነው።

ዘመናዊ የእግረኛ እና የአረንጓዴ ውበትን ያካተተው 50 ሜትር ስፋት ያለው  የአስፋልት መንገድ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት የተየዘለት መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንገዱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅም በሁለት አቅጣጫ እየተገነባ መሆኑን  ጠቅሰዋል።


 

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ መንገዱ ወደ ጁቡቲ ከሚወስደው እና ከነፃ ንግድ ቀጠናና ደረቅ ወደብ መንገዶች ጋር መቆራኘቱ ያለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያጎላዋል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ ቤዛ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ተወካይ ኢንጂነር አህመድ አደም በበኩላቸው ስራው በታቀደለት ጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ወር የመንገዱ አንዱ ክፍል ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን በመጠቆም።


 

የዓመታት የመልካ ጀብዱና የአካባቢውን ማህበረሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት ለ261 የልማት ተነሺዎች በአዲሱ የካሳ ህግ አስፈላጊው ክፍያ መሰጠቱን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት የካሳና የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ጃማይካ ናቸው።

ከካሳ ክፍያ በተጨማሪ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት መዘጋጀቱን ገልፀው የልማቱ ተነሺዎች  በግንባታው ላይ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም አስታውቀዋል።

የመልካጀብዱ የልማቱ ተነሺዎች  ለመንገዱ መሳካትና ለድሬዳዋ የማንሰራራት ዘመን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

በፌደራል መንግስትና በድሬደዋ አስተዳደር የተቀናጀ ጥረት ወደ ግንባታ የተመለሰው ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለድሬዳዋና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የድሬዳዋ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ፣ ፕሮጀክቱ በሚቀጥለው ታህሳስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀመር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም