ናይጄሪያ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ናይጄሪያ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት መርሃ ግብር ናይጄሪያ ቦትስዋናን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂዋ ቺንዌንዱ ለሄዙ በ89ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥራለች።
ናይጄሪያ በጨዋታው ባደረገችው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ነው ጎል ማስቆጠር የቻለችው።
በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የተደረገ ሲሆን ቦትስዋና የዘጠኝ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናይጄሪያን ፈትናታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ናይጄሪያ በስድስት ነጥብ አንድ ጨዋታ እየቀራት ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።
ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ቢሸጋገርም የማጥቃት ድክመቱን ማረም እንደሚጠበቅበት በመገለጽ ላይ ይገኛል።
ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ቦትስዋና ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች።
በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።
አልጄሪያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ እና ቱኒዚያ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ናይጄሪያን ከአልጄሪያ፣ ቱኒዚያ ከቦትስዋና የፊታችን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም የሚደረጉ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ናቸው።
በሶስት ምድብ ተከፍሎ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ሀገራት ለሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ።
ከምድቦቹ ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ተጨማሪ ሁለት ሀገራት ሩብ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።