የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የነጻ ንግድ ቀጣና ቁልፍ የማስተግበሪያ ደንቦች አፅድቀው ወደ ስራ እንዲያስገቡ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የነጻ ንግድ ቀጣና ቁልፍ የማስተግበሪያ ደንቦች አፅድቀው ወደ ስራ እንዲያስገቡ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አባል ህብረት አገራት የአህጉራዊውን ነጻ ንግድ ቀጣና ቁልፍ የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፎችን በማጽደቅ ወደ ስራ እንዲያስገቡ አሳሰበ።
47ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ተጀምሯል።
ስብሰባው “ የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያንና ለዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል ሀሳብ እየተከናወነ ይገኛል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የምክር ቤቱ ዋንኛ የውይይት አጀንዳ የህብረቱ የእ.አ.አ 2026 በጀት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር የህብረቱ ፕሮግራም በጀት በራስ አቅም የመሸፈን ስራ መጠነኛ ለውጥ ቢያሳይም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ተናግረዋል።
ይሁንና እ.አ.አ በ2016 የህብረቱ አባል ሀገራት ወደ አፍሪካ የሚገቡ የተመረጡ እቃዎች ላይ የ0 ነጥብ 2 በመቶ ቀረጥ በመጣል የአህጉራዊውን ተቋም የፋይናንስ አቅም ማጠናከር የሚያስችለውን ውሳኔ ሀሳብ (kigali decision) ቢያፀድቁም በሚፈለገው ደረጃ እየተገበሩት እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ከህብረቱ አባል ሀገራት መካከል 17ቱ ብቻ ስምምነቱን እየተገበሩ ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ የህብረቱን የፋይናንስ ነጻነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎንጎ፣ ሶማሊያ እና ሳሄል ቀጣናን ጨምሮ በአህጉሪቷ ያሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች፣ የሰብዓዊ ቀውሶች እና የደህንነት ችግር አሁን የአፍሪካ ልማት አጀንዳ እንዳይሳካ መሰናክል ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ።
የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የሰላም አስከባሪ ኃይል ያጋጠመው የፋይናንስ እጥረት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ተናግረዋል።
እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል የተደረገው ስምምነት፣ የጋቦን ወደ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መመለስ እና የጊኒ የሽግግር እቅድ ተስፋን የሚያጭሩ መልካም ለውጦች መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ከህብረቱ የሰላም እና ደህነንት ምክር ቤት እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ ትብብሩን በማጠናከር የሰላም ጥረቶችን መደገፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ የህብረቱ አባል ሀገራት የተቋማዊ ሪፎርም ስራን እንዲያፋጥኑንና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማስፈጸሚያ ደንቦችን አፅድቀው ወደ ስራ በማስገባት ለቀጣናዊ ትስስር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
47ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል።
ከምክር ቤቱ ስብሰባ ጎን ለጎን ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የህብረቱ የ7ተኛ የመንፈቅ ዓመት የባለድርሻ አካላት የትብብር ስብሰባ ይደረጋል።
#Ethiopian_News_Agency #Ethiopia #ኢትዮጵያ #ኢዜአ