ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን-የቸሃ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን-የቸሃ ወረዳ ነዋሪዎች

ወልቂጤ፤ ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ)፦ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ በጉራጌ ዞን የቸሃ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
በጉራጌ ዞን "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ በቸሃ ወረዳ ጆካ ቀበሌ ተጀምሯል።
ከቀበሌው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ወርቅነሽ መንጅየ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ስነምህዳርን እና የአፈር ለምነት በመመለስ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘላቸው ነው።
በልማቱ እያገኙት ያለውን ጥቅም ለማሳደግ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ሥራውም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት ለምግብነትና ለደን አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ጀምረናል ያሉት አርሶ አደሯ፣ መርሃ ግብሩ ተፈጥሮን በመጠበቅና በመንከባከብ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆነ ተንከባክበን ለውጤት የማብቃት ልምድን አዳብረናል ያሉት ሌላኛው አርሶ አደር በሃሩ ፍቃዱ ፣ ከልማቱ ተጠቃሚነታቸው እያደገ በመሆኑ ዘንድሮም በችግኝ ተከላው በንቃት በመሳተፍ አሻራቸውን እያኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ደን የመንከባከብ እና ችግኞችን የመትከል ልምድ ቀደም ብሎ በአካባቢያቸው እንዳለ አስታውሰው፣ ይህን ተግባር በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርም አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በበኩላቸው በወረዳው ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተተከሉ ችግኞች የአፈር ለምነት መመለሱንና ምርትና ምርታማነት መጨመሩን ተናግረዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ የማሳደጉ ባህል እየዳበረ መምጣቱን ጠቁመው፣ የሚተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠንም ከ85 ከመቶ በላይ ደርሷል ብለዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ መጀመሩን ገልጸው፣ ችግኞችን ከሰውና ከእንስሳት ንኪክ ነጻ አድርጎ ለማሳደግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ይሰራል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከ37 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ችግኝ ይተከላል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የቀጣይ ትውልድን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ ቡና፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና አፕልን ጨምሮ ሌሎች ለምግብነት የሚውሉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይገኙበታል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በጉራጌ ተፈጥሮን የመንከባከብና የመጠበቅ ባህል እንዳለ ገልጸው ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አጠናክሮ ለማስቀጠል አስችሏል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተከናወኑ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገገሙ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ይህም ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርና ሃገር በቀል ዛፎች ዳግም እንዲያሰራሩ እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል