የባህር ዳር ከተማን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ-አቶ ጎሹ እንዳላማው

ባህር ዳር፤ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦የባህር ዳር ከተማን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።

የከተማዋ አካባቢ ጥበቃ፣ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት በ2017 በጀት ዓመት ያከናወናቸው የተግባር አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ተውውቅ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፥ከተማዋን የበለጠ ውብና ማራኪ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

ከተማዋን ውብ፣ጽዱና ማራኪ በማድረግ የኢንቨስትመንት፣የቱሪዝምና የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህም በከተማዋ አካባቢ ጥበቃ፣ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት አዳዲስ የከተማዋን አካባቢዎች በማልማትና በመንከባከብ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ከተማዋ ለነዋሪው የበለጠ ምቹ እንድትሆን ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ናቸው።

እየተገነቡ ያሉ የአረንጓዴ ልማትና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ባህር ዳር ከተማ ካሏት ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር ተዳምሮ ከተማዋን ለነዋሪዎች፣ ለቱሪስትና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌረዳ አበበ በበኩላቸው፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባለሙያውና በአመራሩ ቅንጅት የከተማዋን የተፈጥሮ ጸጋ አጉልቶ ለማሳየት ተችሏል ብለዋል።


 

በበጀት ዓመቱ የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ 90 ቀናትና በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ የበለጠ ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል።

በተለይም በአካባቢ ጥበቃ ላይ የወጡ ህጎችን በመፈጸምና በማስፈጸም በከተማዋ ከጣና ሐይቅና ዓባይ ወንዝ ጋር የተጣጣመ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

በመድረኩ የከተማዋ አመራሮች፣ የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም