የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ባለፉት ሁለት ዓመታት አበረታች ተግባር አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ባለፉት ሁለት ዓመታት አበረታች ተግባር አከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ባለፉት ሁለት ዓመታት አበረታች ተግባር ማከናወኑን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሊቀ መንበር ሰለሞን ደስታ ገለጹ።
የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ግንዛቤን ለማሳደግ ያለመ ወርክሾፕ ተካሂዷል።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሀገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ እንዲሆን ፈንዱ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡
ለገንዘብ አስቀማጮች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ለፋይናንስ ሥርዓቱ መረጋጋት የላቀ አስተዋጽዖ ከማበርከት ባለፈ የሀገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ለማረጋጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ፈንዱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን በማቀድ የተጣለበትን ኃላፊነት በተሟላ እና በሚፈለገው ደረጃ እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት አረቦን በመሰብሰብ ረገድ አበረታች ስራ መስራቱንም ተናግረዋል።
የአባል ተቋማት ቁጥር 86 መድረሱን ተናግረው 32 ባንኮችና እና 54 ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አባል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ገንዘብ አስቀማጮች እና ባለድርሻ አካላት ስለፈንዱ በቂ ግንዛቤና ዕውቀት እንዲኖራቸው መሰል መድረኮችን በማጠናከር ግንዘቤን ማስፋት እንደሚገባም ነው ያስታወቁት።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) በበኩላቸው ፈንዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ፈንዱን በማደራጀት እና ለሥራ የሚያስፈልጉ የሰው ኃይል እና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት ረገድ አበረታች ሥራ መስራቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም ፈንዱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 13 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር መነሻ እና ዓመታዊ አረቦን መሰብሰቡን ገልጸው፥ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ኢንቨስት በማድረግም ትርፍ እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፈንዱ በቀጣይ የአረቦን የመሰብሰብ አቅሙን እንደሚያሳድግ፣ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ እንደሚያዘመን እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማኅብረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፣ በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ አደጋ ቢያጋጥም፣ አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ስርዓት ነው።