የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃት ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንደሚያስችላቸው የሐመር ወረዳ አርብቶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃት ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንደሚያስችላቸው የሐመር ወረዳ አርብቶ አደሮች ተናገሩ

ሐመር፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃት ዓመቱን ሙሉ በማምረት ኢኮኖሚያ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገው የሐመር ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለጹ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት የመስኖ ልማት አውታሮችን የማስፋፋት ስራዎች ተከናውነዋል።
ይህም አርሶ አደሮች ወቅት ሳይጠብቁ በማምረት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ማገዙን የሐመር ወረዳ አርብቶ አደሮች ገልጸዋል።
ለአብነትም ከ13 ዓመታት በላይ ሲጓተት የነበረው የቁማ መስኖ ፕሮጀክትን ወደ አገልግሎት በማስገባት የአርብቶ አደሩን የግብርና ሥራን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።
በ2004 ዓ.ም የግንባታ ሥራው የተጀመረው ይህ የመስኖ አውታር በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተፈትቶ ወደ ልማት መግባታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገው ከተናገሩት አርብቶ አደሮች መካከል የሐመር ወረዳ የካራ-ቆርጮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አይላ ኩሌምፖና ወጣት ሙላ ፓርኮ የይገኙበታል።
በመስኖ ፕሮጀክቱም በቆሎና ማሽላ በኩታ ገጠም እያለሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ክረምት ከበጋ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዳገዛቸው የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የአንጉዴ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጋዲ ሙጋ ናቸው።
የሐመር ወረዳ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቃላ ቦና በበኩላቸው የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ከ13 ዓመታት በላይ ሲጓተት መቆየቱን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ መጓተቱ በአካባቢው አርብቶ አደሮች ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ 500 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችል የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የቱርሚ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ያዘው አፈወርቅ ናቸው።
የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ሥርአት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ 79 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው የቁማ መስኖ የአካባቢውን አርብቶ አደር ከኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ በማላቀቅ በዘመናዊ እርሻ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይም የቁማ መስኖ ፕሮጀክት ውሀውን ከወንዙ ስቦ ለማውጣት የሚጠቀመውን የነዳጅ ፍጆታ ወደ ኤሌክትሪክ እና ወደ ሶላር የኃይል በመለወጥ በአካባቢው የመስኖ ልማቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 238 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከ32ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም በመስኖ እየለማ ይገኛል።
በመስኖ አውታሮቹም ከ50ሺህ በላይ እማወራና አባውራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።