ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂ ልማት እያከናወነች ነው - ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂ የአካባቢ ጥብቃ ልማት እያከናወነች መሆኗን ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በዚህም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በማቀድ በመላ ሀገሪቱ የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ይገኛል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ተወካዮችና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረዳት ተወካይ ዴቪድ ካርፕ፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ጋር በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ኬቪን ሆጅሶን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመሳተፋቸው ደስታ እንደተሰማቸው ጠቁመው፤ በቀጣይም ተሳትፏቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው ሥፍራዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እንዲጸድቁ ተከታታይ እንክብካቤዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ስራን ጎን ለጎን በማስኬድ የተተከሉ ዕጽዋት ለፍሬ እንዲበቁ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የሴቶችና ህጻናት ቡድን መሪ ምስራቅ መሐመድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም