የድሬደዋ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለማከናወን ይሰራል

ድሬደዋ፣ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፡-የድሬደዋ አስተዳደር  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን  ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለማከናወን እየሰራ  መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

አስተዳደሩ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የተለያዩ ችግኞች ለተጎራባች ክልሎችና ዞኖች እንደሚያሰራጭ ተገልጿል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ አሚን ዑመር ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ከተማ አስተዳደሩ ከምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ለሰላምና ለሁለንተናዊ ልማት በጋራ እየሰሩ  ናቸው።

ይህን እንቅስቃሴ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ይበልጥ ለማጠናከር በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

በተለይም ከምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች እና ከሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን  ጋር በመተባበር   ለድሬደዋ ከተማ  የጎርፍ አደጋ መነሻ የሆኑትን የተራቆቱ ተፋሰሶች በችግኞች የማልበስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ይህን ለማጠናከርም ከቀናት በኋላ በድሬዳዋ የሚጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ላይ  በጋራ እንደሚሳተፉ  ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ የአካባቢ፣የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ለሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እና ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች ችግኞች ይሰራጫሉ ብለዋል።


 

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፋር ክልልም የተለያዩ ችግኞች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም