ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው

ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ገለጹ።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓበይት ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱ በአዲስ አበባ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና ጣልያን የጋራ አዘጋጅነት የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ ከሚደረጉ ተግባራት መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የምግብ ስርዓት ሽግግርን የሚያፋጥኑ የተለያዩ ብሔራዊ መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ይታወቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተተገበሩት የሌማት ትሩፋት የወተት፣ የእንቁላል፣ የስጋ፣ የዓሳና የማር ምርታማነትን በመጨመር ለዜጎች በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ አቅርቦትና ተደራሽነትን ማሻሻል ተችሏል፡፡


 

የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ኢትዮጵያ ታምርት እንዲሁም የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ኢንሼቲቮች ኢትዮጵያ ለሥርዓተ ምግብ መጠበቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አመላካች ናቸው።

ዛሬ እየተካሄደ ያለው ውይይት መገናኛ ብዙሃን ስለጉባዔው ትኩረት ሰጥተው እንዲዘግቡ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ወደ ስራ ገብታ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች በማስመዝገቧም ሁለተኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ስብሰባን ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ መመረጧን ተናግረዋል።

ጉባኤው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ሽፋን በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የዛሬው መድረክም የዚህ አንድ አካል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ወደ ትግበራ ገብታለች ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ሌሎችም ውጤታማ እንዲሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ዘገባዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች ተደራሽ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክም በኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት የሽግግር ጉዞ እውን እንዲሆን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም