ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሥራዎቿን የምታስተዋውቅበት ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሥራዎቿን የምታስተዋውቅበት ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያከናወነቻቸውን ስኬታማ ሥራዎች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ከጳጉሜ 3 እስከ 5/2017 በምታስታናግደውን ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዝግጅት ላይ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውይይት ተደርጓል።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ፍጽም አሰፋ(ዶ/ር) እንዳሉት አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠናከር አለበት።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ብክለት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም በሚደርሰው ተጽዕኖ ግን ከፍተኛ ተጎጂ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በድርቅ፣ በጎርፍ እና በሌሎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች በሚደርስ ጉዳት አህጉሪቱ ከፍተኛ ተጎጂ እንደሆነች ገልፀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል አፍሪካ የምታደርገውን ጥረት በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂና በተለያዩ መስኮች ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ገልጸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የታዳሽ ኃይል፣ የአረንጓዴ ትራንስፖርት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየወሰደች ባለው ተጨባጭ ተግባር ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ እየሰራች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ጭምር በመሆኗ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቋቋም ላይ እየሰራች ያለውን ስራ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮዋን በማጋራት ድጋፍ እያደረገች ነው ብለዋል።
በጉባኤ የተሰሩ ሥራዎችን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ለዘርፉ የፋይናንስ ድጋፍ ለማፈላለግም መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የሀገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢሮ ሃላፊና የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ልዩ ተወካይ ፓርፋይት ኦናንጋ አንያንጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰዳቸው እርምጃዎች ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሃፊ እና ዋና ኢኮኖሚስት ሀናን ሞርሲ(ዶ/ር)፤ በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በተለያዩ ሀገራት እየተደረጉ ያሉ ጅምር ስራዎች አበራታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መፍትሄ አመላካች መሆኑዋን የምታሳይበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ለጉባኤው ስኬትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።