በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው - አቶ ፍቃዱ ተሰማ

ጎንደር፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በፌደራልና በክልሉ መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የከተማውን የልማት ስራዎች ዛሬ ማምሻውን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ፍቃዱ ተሰማ በወቅቱ እንደገለጹት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ለመምጣቱ ማሳያ ናቸው።


 

የክልሉ ህዝብ ሠላም ወዳድና ልማት ፈላጊ መሆኑን በቅርቡ ባካሄዳቸው ሰልፎች መልእክት ማስተላለፉን አመልክተዋል።

የታጠቁ ሀይሎች የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው የሠላምን መንገድ አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው መልእክት ያስተላለፉት።

በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችም የከተማውን ታሪካዊነት የሚያጎሉና የቱሪዝም ማእከልነቱን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት እድሳትና ጥገና ስራ ታሪክን በመጠበቅ የከተማውን የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑንም አብራርተዋል።

የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዳግም ግንባታው የተጀመረው የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ስራ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ስራዎችና የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርም የተሻለ የመልማት እድልና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

አጠቃላይ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ የሁሉም ክልሎች የፓርቲው አመራሮች በተገኙበት በነገው እለት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም