አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠናከር አለበት ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ከጳጉሜ 3 እስከ 5/2017 በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በምታስታናግደውን ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዝግጅት ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ የአለም አቀፍ ተቋማት እና የአጋር አካላት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በዚሁ ወቅት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉት አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠናከር አለበት።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ብክለት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም በሚደርሰው ተጽዕኖ ግን ከፍተኛ ተጎጂ መሆኗን ተናግረዋል።
በዚህም ድርቅ፣ በጎርፍ እና በሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚደርሱ ጉዳቶች አህጉሪቱ ከፍተኛ ተጎጂ እንደሆነች ገልፀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ተቋማት ተጽዕኖውን ለመከላከል አፍሪካ ለምታደርገውን ጥረት በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በተለያዩ መስኮች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ተጨባጭ የሆኑ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ ትራንስፖርት እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ተጨባጭ ውጤት እያመጣች መሆኑን ገልጸው፤ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይም ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ጭምር በመሆኗ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቋቋም ላይ እየሰራች ያለውን ስራ ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮዋን በማጋራት ድጋፍ እያደረገች ነው ብለዋል።